ጃማል-ኡል-አህራር (ጄዩኤ) በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ ከተሰየመው ተህሪክ-ኢ ታሊባን ፓኪታን (ቲቲፒ) ጋር ትስስር ያለው ታጣቂ ቡድን ነው፡፡ በቀድሞ የቲቲፒ መሪ አብዱል ዋሊ በነሐሴ 2006 ዓ.ም. የተመሰረተው ጄዩኤ በፓኪስታን ሲቪል ሰዎችን፣ ኃይማኖታዊ አናሳ ቡድኖችን፣ ወታደሮችን እና ሕግ አስከባሪዎችን ዒላማ ያደርጉ በርካታ ጥቃቶችን ፈጽሟል፡፡ በነሐሴ 2007 ዓ.ም. ጄዩኤ በፑንጃብ ፓኪስታን ለተፈጸመው እና የፑንጃብ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስተርን ለሞት ለዳረገው ጥቃት ኃላፊነቱ ወስዷል፡፡ ጄዩኤ በመጋቢት 2008 ዓ.ም. በፔሻዋር ለሁለት የዩናይትድ ስቴትስ ቆንስላ ሠራተኞች ሞት ምክንያት የሆነውን ጥቃት ፈጽሟል፡፡ በመጋቢት 2008 ዓ.ም. መጨረሻ፣ ጄዩኤ በላሆር፣ ፓኪስታን በሚገኝ በጉልሻን-ኢ-ኢቅባል መዝናኛ ፓርክ ላይ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ፈጽሞ ከ70 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ ከእነርሱ መካከል ከግማሽ ያህል የሚሆኑት ሴቶች እና ሕጻናት ነበሩ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡
በሐምሌ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጃማል-ኡል-አህራር (ጄዩኤ)ን ልዩ አለም አቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚህም መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የጃማል-ኡል-አህራር (ጄዩኤ) ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከጃማል-ኡል-አህራር (ጄዩኤ) ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡