ወሮታ ለፍትሕ ስለ ጀሃድ ሰርዋን ሞስጣፋ፣ በሌላ ስሙ አንዋር አል-አምሪኪ እና ኢምር አንዋ መረጃ ለሚሰጥ እስከ $10 ሚሊዮን ወሮታ ይከፍላል፡፡ ሞስጣፋ የአሜሪካ ዜጋ እና የቀድሞ የካሊፎርኒያ ነዋሪ ሲሆን፣ በዩናይትድ ስቴትስ ሽብርተኛ ተብሎ በተሰየመው ድርጅት አል-ሸባብ ውስጥ የአመራር ሚናዎች ይዟል፡፡ ይህ ግለሰብ የአሜሪካ ዜጋ ሆኖ በውጭ አገር ከሽብርተኛ ድርጅት ጎን ተሰልፎ የሚዋጋ ከፍተኛ ኃላፈነት ላይ የሚገኝ ሰው ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
ሞስጣፋ በሳንዲያጎ ኖሯል፤ በዚያም ከኮሌጅ ተመርቋል፤ በ1997 ዓ.ም. ወደ ሶማሊያ ተዘዋወረ፡፡ በግምት በ2000 ዓ.ም. አካባቢ ከአልሸባብ ጋር ከመቀላቀሉ በፊት በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ተሳትፏል፡፡ ከአል-ሸባብ ጋር ሞስጣፋ በበርካታ ቁልፍ ኃላፊነቶች ላይ ሰርቷል፡፡ ካገለገለባቸው ኃላፊነቶች መካከል በቡድኑ የሥልጠና ካምፖች ወታደራዊ መምህር ወይም አሰልጣኝ፣ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ተዋጊዎች መሪ፣ በቡድኑ የሚዲያ ክንፍ ውስጥ መስራት፣ በአል-ሸባብ እና በሌሎች ሽብርተኛ ድርጅቶች መካከል አገናኝ ሆኖ መስራት እና ቡድኑ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም የፈንጂ አጠቃቀምን መምራት ይገኙባቸዋል፡፡
በመስከረም 29 ቀን 2002 ዓ.ም. ሞስጣፋ ለሽብርተኞች የማቴሪያል ድጋፍ ለማድረግ በመመሳጠር፣ ለአል-ሸባብ የማቴሪያል ድጋፍ ለማድረግ በመመሳጠር እና ለአል-ሸባብ የማቴሪያል ድጋፍ በመስጠት ምክንያት በካሊፎርኒያ ደቡባዊ ዲስትሪክት ክስ ይመስረትበት የሚል ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡ በኅዳር 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በፌዴራል ፍርድ ቤት የቀረበ ክስ ሞስጠፋ ከሽብርተኝነት ጋር ተያያዥ በሆኑ ጥፋቶች ክስ ይመስረትበት ተብሏል፡፡ ሞስጣፋ በኤፍቢአይ እጅግ ተፈላጊ ሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ ስሙ ተካቷል፡፡