አል-ኑስራህ ፍሮንት (ኤኤንኤፍ) የተቋቋመው በ2003 ዓ.ም. በኢራቅ የአል-ቃዒዳ መሪ አቡ በከር አል-ባግዳዲ የኤኤንኤፍ መሪ ሙሐመድ አል-ጃውላኒ ወደ ሶሪያ ሄዶ የሽብር ሕዋሳትን እንዲያደራጅ በላከው ጊዜ ነበር፡፡ በሚያዝያ 2005 ዓ.ም. አል-ዳውላኒ ለአል–ቃዒዳው መሪ አል-ዛዋሂሪ ታማኝነቱን ገለጸ፡፡ ኤኤንኤፍ ከኤኪውአይ ተገንጥሎ ራሱን የቻለ አካል ሆነ፡፡ በጥር 2009 ዓ.ም. ኤኤንኤፍ ከበርካታ ሌሎች አክራሪ ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር ተዋሀዶ ሃያት ታህሪሪ አል-ሻም (ኤችቲኤስ) የሚባል ድርጅት አቋቋሙ፡፡ ኤኤንኤፍ አሁንም በሶሪያ የአል-ቃዒዳ ተባባሪ ድርጅት ሆኖ ይገኛል፡፡
ኤኤንኤፍ ግቡ የሶሪያን መሪ አሳድን ከሥልጣናቸው ማንሳት እና በሱኒ ኢስላማዊ መንግሥት መተካት መሆኑን ገልጾአል፡፡ ኤኤንኤፍ በሰፊው የሚገኘው በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ሲሆን፣ በዚያም የተወሰነ ግዛት ይቆጣጠራል፡፡ በዚያም በተቃዋሚ ኃይልነት በመንቀሳቀስ ላይ ነው፤ በአካባቢው መንግሥት እና በውጭ አገራት በሚፈጸሙ የመመሳጠር ተግባራትም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ኤኤንኤፍ በመላው ሶሪያ ንጹሃንን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች ፈጽሟል፡፡
በግንቦት 07 ቀን 2006 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጀመሪያ ኤኤንኤፍን በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በማለት በተሻሻለው የኢምግሬሽን እና ዜግነት ሕግ፣ በክፍል 219 መሠረት ሰይሞታል፡፡ ቀደም ብሎ በግንቦት 06 ቀን 2006 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤኤንኤፍን ልዩ አለምአቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚህም መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የኤኤንኤፍ ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከኤኤንኤፍ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበው ኤኤንኤፍ ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡