አል-ቃዒዳ በዓረብ ባሕረሰላጤ (ኤኪውኤፒ) በየመን የሚንቀሳቀስ፣ የየመን እና የሳውዲ ሽብርተኞች ከተዋሃዱ በኋላ የተፈጠረ ድርጅት ነው፡፡ ኤኪውኤፒ ካስቀመጣቸው ግቦቹ መካከል በዓረብ ባሕረሰላጤ እና በሰፊው መካከለኛ ምሥራቅ ኢስላማዊ መንግሥት ወይም ካሊፌት መመስረት እና የሸሪዓ ሕግን ተግባራዊ ማድረግ ይካተል፡፡ ኤኪውኤፒ በዓረብ ባሕረሰላጤ እንዲሁም በውጭ አገራት የአሜሪካን እና የምዕራቡን ዓለም ጥቅሞች ዒላማ በማድረግ ተንቀሳቅሷል፡፡ ይህ ቡድን ለበርካታ የሽብር ጥቃቶች ኃላፊነት ወስዷል፤ ከእነርሱም መካከል በጥር 2007 ዓ.ም. የተፈጸመው፣ ለ12 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው በፓሪስ በቻርሊ ሄብዶ ጋዜጣ መሥሪያ ቤቶች ላይ የተፈጸመው ጥቃት አንዱ ነው፡፡
ኤኪውኤፒ የኤኪው ተባባሪ ድርጅት ሲሆን፣ ጥቃቶችን ለማቀድ የኤኪውኤፒ መሪ ከኤኪው አመራር ጋር አብሮ ይሰራል፡፡ አል-አሪሲ የተባለው የኤኪውኤፒ የቦምብ ጥቃት አድራሽ በ2004 ዓ.ም. በገና በዓል ቀን የተፈጸመውን የውስጥ ሱሪ የአየር መንገድ ቦምብ ጥቃት ነድፏል፤ በተጨማሪም በአጓጓዦች አማካኝነት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የፕሪንተር ቦምቦች ልኳል፡፡
በጥር 11 ቀን 2002 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤኪውኤፒን በተሻሻለው የኢምግሬሽን እና ዜግነት ሕግ፣ በክፍል 219 መሠረት በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት እንዲሁም ልዩ አለምአቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚህም መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የኤኪውኤፒ ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከኤኪውኤፒ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበው ኤኪውኤፒ ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡