ወሮታ ለፍትሕ በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ ስለተሰየመው የአል-ሸባብ ቁልፍ መሪ ማሊም ሳልማን መረጃ ለሚሰጥ እስከ $3 ሚሊዮን ወሮታ ይከፍላል፡፡ ሟች የአል-ሸባብ መሪ አሕመድ አብዲ ጎዳኔ፣ ሳልማን የአልሸባብን የአፍሪካ የውጭ አገራት ሽብርተኛ ተዋጊዎችን እንዲመራ መረጡት፡፡ ሳልማን፣ በሌላ መጠሪያ ስሙ ማሊም ሳልማን አሊ እና አመር ሳልማን በአፍሪካ ውስጥ ቱሪስቶችን፣ የመዝናኛ ተቋማት እና አብያተ ክርስቲያናትን ዒላማ ባደረጉ ጥቃቶች ውስጥ ተሳትፎ ነበረው፡፡ በዋናነት ከሶማሊያ ውጪ በሚካሄዱ ኦፕሬሽኖች ላይ የሚያተኩር ቢሆንም እንኳን፣ ሳልማን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚላኩ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ተዋጊዎች ያሰለጥናል፡፡ በመስከረም 04 ቀን 2007 ዓ.ም.፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳልማንን ልዩ አለምአቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚህም መሰረት ሌሎች እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የሳልማን ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከሳልማን ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበው አል-ሸባብ ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡