ወሮታ ለፍትሕ ስለ ሙሃመድ አል-ጃውላኒ በሌላ ስሙ አቡ ሙሀመድ አል-ጎላኒ እና ሙሃመድ አል-ጁላኒ እና አሽራፍ ናኢም ማንሱር መረጃ ለሚሰጥ እስከ $10 ሚሊዮን ወሮታ ይከፍላል፡፡ አል-ጃውላኒ በሶሪያ የአል-ዒዳ ተባባሪ ድርጅት የሆነው የአል-ኑስራህ ግንባር (ኤኤንኤፍ) መሪ ነው፡፡ በጥር 2009 ዓ.ም. ከበርካታ ሌሎች አክራሪ ተቃዋሚ ቦድኖች ጋር በመቀላቀል ሃያት ታህሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ) የተባለ ድርጅት አቋቁሟል፡፡ አል-ጃውላኒ የኤችቲኤስ መሪ ባይሆንም እንኳን፣ የኤችቲኤስ ዋነኛ አካል የሆነው ከአል-ቃዒዳ ጋር ግንኙነት ያለው ኤኤንኤፍ መሪ ነው፡፡
በአል-ጃውላኒ አመራር ስር፣ ኤኤንኤፍ በመላው ሶሪያ በርካታ ጥቃቶች ፈጽሟል፤ አብዛኞቹ ጥቃቶች ደግሞ ንጹሃንን ዒላማ ያደረጉ ነበሩ፡፡ በሚያዝያ 2007 ዓ.ም. ኤኤንኤፍ በሶሪያ ከሚገኝ አንድ የጥበቃ ስፍራ በግምት 300 የሚሆኑ የኩርድ ሲቪሎችን አግቶ በኋላ ለቋቸዋል፡፡ በሰኔ 2007 ዓ.ም.፣ ኤኤንኤፍ በሶሪያ የኢድሊብ ክፍለ አገር የድሩዜ መንደር በሆነው ቃልብ ላውዘህ 20 ለሚሆኑ ነዋሪዎች ግድያ ተጠያቂ ነው፡፡
በሚያዝያ 2005 ዓ.ም. አል-ጃውላኒ ለአል-ቃዒዳ እና ለመሪው አይመን አል-ዛዋሂሪ ያለውን ታማኝነት ገልጾአል፡፡ በሐምሌ 2008 ዓ.ም.፣ አል-ጃውላኒ በአንድ ኦንላይን ቪድዮ ለአል-ቃዒዳ እና አል-ዛዋሂሪ ያለውን አድናቆት ገልጾዋል፤ በዚሁ ቪድዮ ላይ ኤኤንኤፍ ስሙን ወደ ጃብሃት ፋት አል ሻም (“የምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን ድል ግንባር”) እንደሚቀይር ገልጾዋል፡፡
በግንቦት 08 ቀን 2005 ዓ.ም.፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አል-ጃውላኒን ልዩ አለምአቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚህም መሰረት ሌሎች እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የአል-ጃውላኒ ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከአል-ጃውላኒ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበው ኤኤንኤፍ ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡