ላሽካር-ኢ ታዪባ (ኤልኢቲ)፣ በሌላ ስሙ አርሚ ኦፍ ዘ ራይቺየስ (የጻድቃን ጦር)፣ በ1970ዎቹ በፓኪስታን የተመሠረተ ሽብርተኛ ድርጅት ነው፡፡ ኤልኢቲ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ጥቃቶች ጨምሮ ሌሎችን ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ በሕንድ ወታደሮች እና የሲቪል ዒላማዎች ላይ ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ ይህ ቡድን በአፍጋኒስታን ውስጥ ጥምር ጦር ላይም ጥቃት ፈጽሟል፡፡ ኤልኢቲ በኅዳር 2006 ዓ.ም. በሙምባይ ለደረሰው፣ የአሜሪካ ዜጎችን ጨምሮ 166 ሰዎችን ለገደለው እና ከ300 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ላቆሰለው ጥቃት በኃላፊነት ይጠየቃል፡፡
በታኅሳስ 17 ቀን 1994 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላሽካር-ኢ ታዪባ (ኤልኢቲ)ን በተሻሻለው የኢምግሬሽን እና ዜግነት ሕግ፣ በክፍል 219 መሠረት በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት ብሎ ሰይሞታል፡፡ ቀደም ብሎ በታኅሳስ 11 ቀን 1994 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤልኢቲን ልዩ አለም አቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚህም መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የኤልኢቲ ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከኤልኢቲ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበው ኤልኢቲ ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡