ሂዝባላህ በሊባኖስ የተመሠረተ ሽብርተኛ ድርጅት ሲሆን፣ ከኢራን የጦር መሣሪያዎች፣ ሥልጠና እና ገንዘብ ያገኛል፤ ኢራን በ1976 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሽብርተኝነት ስፖንሰር መንግሥት በሚል ተሰይሟል፡፡ ሂዝባላህ ሰፊ የሽብርተኞች ኔትወርክ ያለው ሲሆን፣ ለበርካታ ሰፋፊ ጥቃቶችም ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ ከእነርሱም መካከል፡- በ1976 ዓ.ም. በቤይሩት የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት፤ በ1977 ዓ.ም. የተፈጸመው የቲደብልዩኤ በረራ 847 ጠለፋ ይገኙባቸዋል፡፡ እንዲሁም ሂዝባላ በ1984 ዓ.ም. በአርጀንቲና የእስራኤል ኤምባሲ እና በ1986 ዓ.ም. በአይሁድ ሙችዋል ኤይድ ማኅበር፣ ቦነስ አይረስ ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ኃላፊነቱ የሂዝባላህ እና የኢራን መንግሥት ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ይታመናል፡፡ በ2004 ዓ.ም. የሂዝባላ አባላት በቡልጋሪያ ስኬታማ የጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ፈጽመዋል፡፡ ሕግ አስከባሪ አካላት እንደ አዘርባጃን፣ ሳይፕረስ፣ ግብጽ፣ ኩዌት፣ ናይጄሪያ፣ ፔሩ እና ታይላንድ ባሉ አገራት በሂዝባላህ ሽብርተኛ ድርጅት የተሞከሩ እና የታቀዱ የሽብር ጥቃቶችን ለመቀልበስ ችለዋል፡፡
በመስከረም 28 ቀን 1990 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሂዝባላህን በተሻሻለው የኢምግሬሽን እና ዜግነት ሕግ፣ በክፍል 219 መሠረት በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት ብሎ ሰይሞታል፡፡ በኋላም በጥቅምት 21 ቀን 1994 ዓ.ም. ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሂዝባላህ ልዩ አለምአቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚህም መሰረት ሆነው በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የሂዝባላህ ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከሂዝባላህ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበው ሃማስ ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡